ከጫት ሱስ መላቀቅ

በአገራችን በሚልዮን የሚቀጠሩ ወንዶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አዋቂዎች ጫት ይቅማሉ፡፡ ጫት ማብቀልም ሆነ መቃም በአገራችን ከተጀመረ በሺህ የሚቆጠር አመታት ሲያስቆጥር በአሁኑ ጊዜ ከተጀመረበት ከምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ወደ ሌላው በመስፋፋት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና ከተማዎች በሰፊው በጥቅም ላይ ውሏል፡፡ የበለጠም እየተስፋፋ ነው፡፡ ምንም እንኳን በአንዳንድ ባለሥልጣናትም ሆነ በሃይማኖት መሪዎች ቢወገዝም፣ ስርጭቱንም ለመቀነስ ሙክራ ቢደረግም ጫት መቃም የበለጠ አየተስፋፋ ነው፡፡ በባህል በሐይማኖት ውስጥ ቦታ የተሰጠው መደበኛ ልማድ ከመሆኑም በላይ ለዘመናት የተለያዩ በሽታዎችን ለመፈወሻ እንደ ባህል ሕክምና ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ አሁንም እያገለገለ ነው፡:

ጫትን በለጋነቱ ለሚቅሙትም ሆነ አድርቀው በሻይ መልክ ለሚጠጡት ሃይልና ብርታትን ይሰጣቸዋል፣ አንቅልፋቸውን ፣ ድካማቸውን ያስወግድላቸዋል፤ በአራሳቸው አንዲያምኑ እንዲደሰቱ ያደርጋቸዋል፣ ለተማሪዎች በደንብ እንዲያጠኑ ፣ ትምህርት አንዲገባቸው ይረዳቸዋል፤ ለሠራተኞቹም ሥራቸውን በቅልጥፍና እንዲሰሩ ያግዛቸዋል፡፡ የምግብ አጥረት ባለበት ሁኔታ ደግሞ የምግብ ፍላጐትን በመቀነስ የመራብ ስሜትን ይቀንሳል፡፡ ከወዳጅ ከዘመድ ጋር ያቀራርባል፤ ያስተሳስራል፡፡ አነዚህን ስሜቶች ጫት ተጠቃሚዎቹን እንደሚሰሟቸው በአገራችንም ሆኑ በሌላ አገሮች የተጠኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ የጫት ልማድ ያለው በአፍሪካና በአረብ አገሮች በመሆኑና በጣም ላደጉ አገሮች አንደችግር ስለማይቆጠር በሌሎች እፆች ላይ አንደተደረገው አይነት ሰፊና ጥልቅ ጥናቶች አልተደረጉም፡፡

በጫት ውስጥ ያለውና ለሱስ ምክንያት የሚሆነው ካቲዮኒን የሚባል ኬሚካል ነው:፡: ይሄ ኬሚካል በደማችን ውስጥ ሀይልና ንቃት የሚሰጡ ኬሚካሎችን (ካትኮላሚንና ሴሮቶኒን) ሰውነታችን እንዲለቅ ያደርጋል፡፡ ይሄንን ለማድረግ የሚችሉት በአንጐል ላይ በሚያመጡት ለውጥ ሲሆን አንጐልም አነዚህ አነቃቂ ኬሚካሎች ወደ ደም አንዲረጩ አስፈላጊውን መመሪያ ለሚመለከታቸው የሰውነት ክፍሎች ስለሚሰጥ ነው፡፡ አነዚህ አነቃቂ ኬሚካሎች ደግሞ አእምሮን ማነቃቃት፤፤ በተጨማሪ ለአካል ብርታትና ቅልጥፍናም ይሰጣሉ፡፡ ከጫት ሌላ አነዚህን የሰውነት አነቃቂ ኬሚካሎች መረጨት የሚጨምሩ ሌሉች አፆች ሆኑ መድሐኒቶች በአለም-አቀፍ ሆነ አገር አቀፍ የስፖርት ውድድሮች የሚከለከሉበት አንደኛው ምክንያት ይሄ ነው፡፡

የጫት ቅጠልን ለረዥም ጊዜ በአፍ ውስጥ በመያዝ ፣ ለማዋፃህድ ስኳር ወይም ጣፋጭ መጠጦችን መውሰድ፣ በጥርስ ፤ በአፍ፣ አና በጨጓራ ላይ የጤና ችግር ከማምጣታቸው ሌላ ጫት በአአምሮ ጤና ላይ የሚከተሉትን ችግሮችም ሊያስከትል ይትላል፡፡

  • የካቲዮኒን ሱስ፡- ለሥራ፣ ለትምህርት..ወዘተ የሚወሰደው ጫት መጠን ሰውነትዎ አየለመደው ሲመጣ ከዚያ በላይ እንዲወስዱ ይገደዳሉ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያስፈልግዎት የጫት መጠን አየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይሄንን ካላገኙ ደግሞ በሥራዎና በትምህርትዎ ላይ ችግር ሊፈጥረብዎ ይችላል
  • የካቲዮኒን ስካር፡:- በአንድ ጊዜ በብዛት ጫት መቃም በደም ውስጥ የካቲዮኒን ብዛት ከፍ በማድረግ ምርቃና ሊያመጣ ይችላል፡፡ እንደዚሁ ጫት ተፈልቶ እንደ ሻይ (ሀውዛ) በሚጠጣበት ሁኔታ ብዙ ከተጠጣ ብዙ ካቲዮኒን ወደ ደም ውስጥ ገብቶ ስካር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ጭንቀት፣ ንዴት ፣ ከመጠን በላይ መፈንጠዝ ፣ ክፉኛ መጠራጠር፣ የተዛባ አስተሳሰብ፤፤ ሥራና ትምህርትን በአግባቡ ለመከታተል ያቅታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አይን መፍጠጥ፣፤፣ የልብ ትርታ መፍጠን፣ የደም ግፊት መጨመር፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ማላብ ፣ የጡንቻዎች ዝልፍልፍ ማለት ሊከተል ይችላል፡፡ ስካሩ ምርቃናውን ካጠነከረ ደግሞ መፍዘዝ ፣የት አንዳሉ አለማወቅ፣ ራስን አስከመሳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ እነዚህ የስካር ስሜቶች ጫቱ ከቆመ ከአንድ ከሁለት ቀን በኋላ ይጠፋሉ
  • የጫት ማቆም የሚያስከትላቸው ሕመሞች፡- የጫት ሱስ ያለባቸው ሰዎች ጫት ሲያቆሙ የመጨነቅ ፣ የመደበት ፣ የመንቀጥቀጥ ስሜቶች ሊሰማቸው ይችላል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ ራስምታት፣ ድካም፣ ማላብ ፣ ቁርጥማት ፣ የሆድ ቁርጠት፣ ከፍተኛ ረሀብ አና ቅዠት ይኖራቸዋል፡፡ የመደበት ስሜቱ ከጠነከረ አንዳንዶቹ ራሳቸውን ለማጥፋት ማሰብና ማቀድ አስከ መፈፀምም ሊደርሱ ይችላሉ
  • ጫት የሚያስከትለው የአእምሮ ቀውስ፡- አልፎ አልፎም ጫት መቃም አንዳንድ ሰዎችን ሊያሳብድ ይችላል፡፡ የአእምሮ ቀውስ የጀመራቸው የሆነ (በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ) ጥርጣሬ በሰዎች በድርጅቶች....ወዘተ ላይ ይኖራቸዋል፡፡ የማይታይ ነገር ይታያቸዋል፣ የሌለ ድምፅ ይሰማቸዋል፣ ያንቀዠቅዣቸዋል፣ የወሲብ ፍላጐታቸው ድርጊታቸው ከመጠን በላይ ይጨምራል፡፡ ይህ የአአምሮ ቀውስ ለጥቂት ቀናት ያህል ብቻ የሚቀጥል ቢሆንም በዚህ አጭር ጊዜ አራሳቸውንም ሆነ ሌላ ሰው ሊጐዱ ህይወት አስከማጥፋትም ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ ለአጭር ጊዜ ለአእምሮ ቀውስ ህክምና ቢያስፈልጋቸውም ጫቱን አስከመጨረሻ ከማቆም በስተቀር ሌላ ጥሩ አማራጭ የለም
  • ጫትና ወሲብ፡- ጫት ከተወሰደ በኋላ የወሲብ ፍላጐት ሊጨምር፣ የወንድ ብልትም ሊቆም ይችላል፡፡ አየቆየ ሲሄድ ግን ወሲብ ፍላጐትም ሆነ ችሎታ እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል፡፡
  • ጫትና ጭንቀት:- ጫት መውሰድ ሆነ ማቆሙ የጭንቀት በሽታ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ከዚህ በፊት የመርበትበት በሽታ፣ ከፍተኛ ፍርፃት አና ሌላም የጭንቀት በሽታዎች ያሏቸው ሰዎች በጫቱ ምክንያት ህመሞቻቸው ሊያገረሹባቸው ይችላሉ
  • ጫትና እንቅልፍ፡- በጫት ምርቃና ውስጥ ያሉ ሰዎች አንቅልፍ መተኛተት ያቅታቸዋል፡፡ ከተኙም በቀላሉ ይነቃሉ፣ ብዙም አይተኙም፡፡: በአንፃሩ ደግሞ ጫት ያቆሙ ሰዎች አንቅልፍ ሊበዛባቸው ይችላል፤ ቅዥታቸውም ከባድ ፣ ልክ የአውን የሚመስልና የሚያስፈራ ሊሆን ይችላል

ከጫት ሱስ ለመላቀቅ

  • በመጀመሪያ በጫት ውስጥ ያለው ካቲዮኒንን ሱሱን አንዳመጣብዎት ይገንዘቡ
  • ጫት ለማቆም የሚቻል ቢሆንም ቀላል እንዳልሆነ ይረዱ
  • ለምን ማቆም አንደፈለጉ በደንብ ይወቁት ፣ በግልፅ ያስቀምጡት፡፡ ለምሳሌ ጥርስዎን ስለአበላሸብዎት ከሆነ ይሄንኑ በግልፅ ጽፈውት ሁልጊዜ ከሚያዩበት ቦታ (ለምሳሌ ፊት ማያ መስታዎት ጐን) ያስቀምጡት
  • የሚወስዱትን የጫት መጠን ለመቀነስ ይሞክሩ፡፡ ለወትሮው ከሚገዙት መጠን አነስ አድርገው ይግዙ
  • ሙሉ ለሙሉ የሚያቆሙበት ቀን ይቁረጡ፡፡ ይሄንንም ለዘመድ/ለወዳጅ ያስታውቁ፡፡ ይህንን ቁርጠኛ ሃሳብዎን እንዲደግፍዎት በጥሞና ይጠይቁ፡፡ ሊያሰተጓጉልዎት ለሚፈልጉት ፊት አይስጡ
  • የሚወስዱት መጠን አየቀነሱ እየቀነሱ በዚያች በተቆረጠችበት ቀን ጫት መቃም ያቁሙ፡: ለሁለት ለሦስት ሳምንት እየቀነሱ ከመጡ ጫት ማቆም ብዙ አይጫንዎትም
  • ያለጫት የሚያሳልፋቸውን ቀኖች ይቁጠሩ፡፡ አየጨመሩ ሲሄዱ ለእአራስወዎ ምስጋና ይስጡ፡፡ በማቆምዎ ምክንያት የሚያገኗቸውን ጥቅሞች ያስቡ፡፡ ጥርስዎና አፍዎ ጤነኛ ይሆናሉ፡፡ እንቅልፍዎ ይስተካክላል፤፣ ሱሰኛ መሆን ይቀርልዎታል፣፤ ገንዘብ ያተርፋሉ
  • በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ከዚህ በፊት የሚቅሙባቸው ቦታዎች፣ አካባቢዎች፣ ክፍሎች ጋር አይድረሱ፡፡ ፍላጐቱ ከጠነከረብዎት ያ አስኪያልፍ ድረስ ሌላ የሚያስረሳ ነገር (ለምሳሌ የአካል አንቅስቃሴ) ያድርጉ
  • በጫት በመቃም የሚያሳልፉትን ጊዜ ሌላ ሥራ ይስሩበት ፣ የአካል አንቅስቃሴ በየቀኑ ያድርጉ፡፡ ከሱስ ለመላቀቅ ይረዳዎታል፡፡ ለጤናዎም ጥሩ ነው
  • ጫት በማቆምዎ የጭንቀት፣ የመረበሽ፣ የመደበት አና ሌላ የአእምሮ ችግር ከጠናብዎት ወደ አእምሮ ሐኪም ይሂዱ
  • አንድ ሁለት ቀን ከተሳሳቱና ጫት ከወሰዱ ተስፋ አይቁረጡ፡፡ መሳሳትዎን ከሚያስቡ ይልቅ እስከዚያ ቀን ድረስ ሳይወስዱ መቆየትዎን እንደ ድል ይቁጠሩ፡፡ ዋናው ነገር ተስፋ ሳይቆርጡ አንደገና ይሞክሩ፡፡ ሐሳብዎ ይሳካልዎታል

Add new comment