በማዘጋጃ ቤት በኩል በቧንቧ የሚያገኙት ውሃ ከማከፋፈያው ቦታ አስፍላጊው የማጣራት እርምጃዎች ስለሚደረግበትና በየጊዜው ስለሚመረመር ለጤና ጐጂ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከማከፋፈያ ቦታ አርስዎም ጋር የሚደርሰው በተቀጣጠሉ ረዥም ባንቧዎች በመሆኑ በመንገድ ላይ ሊበከልና ሊበላሽ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ቧንቧዎቹ ለዘመናት ያልተቀየሩና ያረጁ ከሆኑ ከነርሱ ላይ የሚነሳው ኬሚካል ውሃውን ሊያበላሸው ይችላል፡፡ በተጨማሪም ቧንቧዎቹ በሚያልፉቧቸው መንገዶች ቦታዎች የአይነምድር ክምችቶች ካሉና ቧንቧዎቹ የተቀደዱ ከሆነ የሚጠጡት ውፃ በአይነምድር ሊበከል ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ በጤና ላይ ከፍተኛ ችግር ያስከትላል፡፡
ከጉድጓድ የሚገኙ ውሃዎችም ከአይነምድር መበከል ከራቁና አስፈላጊው ምርመራ በየጊዜው ከተደረገላቸው ሊጠጡ ይችላሉ፡: በአንዳንድ አካባቢዎች (በተለይም በስምጥ ሸለቆ ውስጥ) በውሃ ውስጥ ያለው የፍሎሪን ኬሚካል መጠን ከፍተኛ ስለሆነ በጥርስ ላይና በአጥንት ላይ ጉዳት በማምጣት ለብዙ ሰዎች የጤና ጠንቅ ሆኗል፡፡
በሌሎች አካባቢዎች ከፋብሪካዎች፤ ከግብርና እና ከድርጅቶች የሚወጡ ፍሳሾች ቀጥታውን በወንዞችና በሃይቆች የሚለቀቁበት ሁኔታ ካለ አነዚህም የሚያመጡት የውሃ ብክለት ለጤና ከፍተኛ ጉዳት ይኖረዋል፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች ፍሳሽ ቀጥታውን እንኳን ወደ ወንዝ/ሐይቅ ባይለቀቅም ከተጠራቀሙበት ቦታ በዝናብ ወይም በማንጠባጠብ (ለምሳሌ ማጠራቀሚያው ከአረጀ ወይም ከተጐዳ) በማዠት የሚጠጣ ውሃ ክምችቶችን ሊበክል ይችላል፡፡
በሱቆች፣ በምግብና በመጠጥ ቤቶች እና በሆቴሎች የሚሸጡ የምንጭ፣ የጉድጓድ፣ የጠበል፤ ወዘተ ውሃዎች በየጊዜው የሚመረመሩ ከሆነና ክምችታቸው ከጐጂ ኬሚካሎችና ከአይነምድር ክምችቶች የራቀ ከሆነ ለጤና ጐጂነት የላቸውም፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ይመረመሩ እንደሆነ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡
ለቧንቧውም ሆነ ታሸገው ለሚሸጡ ውሃዎች ጎጂ መሆን አለመሆን ቁጥጥር የሚያደርጉት መንግስታዊ ድርጀቶች ስለሆኑ የነርሱ ችሎታ፣ ጥንካሬና ንቃት ለጤንነት ወሳኝ ነው፡፡
በቤትዎና በመሥሪያ ቤትዎ ግን አንዳንድ እርምጃዎችን በማድረግ የአርስዎንና የቤተሰብዎን ጤና ለመጠበቅ ይችላሉ
የቧንቧውም ሆነ ከሱቅ የገዙት ውሃ በጤናዎ ላይ ችግር ካመጣብዎት ለሚመለከተው ባለስልጣን መሥሪያ ቤት ያስታውቁ፤ ያሳስቡ፤ የመስተካከል እርምጃ ሊወሰድ ይችላል
