አርስዎ ሳይፈልጉ ሳይስማሙ፣ ያለፍቃድዎ የሚደረግብዎ የወሲብ ግንኙነት ወይም ሌላ አይነት ወሲባዊ ጥቃት የተለያዩ አይነቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የወሲብ ግንኙነት ሲባል በወንድ ብልት፣ ጣት ወይም በተለያየ ቁሳቁስ የተካሄደ ሊሆን ይችላል፡፡: ከዚህም ሌላ በኃይል መሳም፣ ሰውነትዎን ማሻሸት/መንካት፣ ወሲብ አዘል የሆኑ አነጋገሮች፣ አስተያየቶች፣ አመለካከትንም ይጨምራል፡፡ በሥራዎ አካባቢም ከአለቃምዎ፣ በተቀጣጣሪዎ፣ በአስተማሪዎ፤ ወዘተ የሚደረግ ማስፈራራት፣ የማስገደድ ሙከራዎችንም ይጨምራል፡፡
በአገራችን የሴቶች መብት በሰፊው በሚረገጥበት ሁኔታ፣ ሴቶች ከወንዶች ዝቅ ተደርገው በሚታዩበት ሁኔታ፣ እራሳቸው ሴቶችም ቢሆኑ በወንዶች ሲጠቁ በዝምታ መቀበልን፣ አንደ ዕጣ ፋንታ መቁጠርን፣ አንዲያውም ለደረሰባቸው ጥቃት አራሳቸውን እንደጥፋተኛ የመቁጠር ዝንባሌ የሚያሳዩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡
አስገድደው የወሲብ ግንኙነት የሚያደርጉብዎ ወንዶች የሚያውቋቸው የቅርብ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አስገድደው የሚደፍርዎ ባለቤትዎ፣ የፈቷቸው የቀድሞ ባለቤትዎ፣ የወንድ ጓደኛዎ፣ አለቃዎ፣ የሥራ ባልደረባዎ፣ የቅርብ ወይም ሩቅ የሥጋ ዘመድዎ፤ ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይ 18 ዓመት ያልደረሱ ልጆች/ወጣቶች ከአባቶቻቸው/ ከወንድሞቻቸው አና ከሌሎች ዘመዶቻቸው የወሲብ ጥቃት ሊደርስባቸው ይችላል፡፡
ብዙዎቻችን አስገድዶ መድፈርንና ሌሎች የወሲብ ጥቃቶችን የምናያይዘው ከማይታወቁ፣ አይተናቸው ከማናውቅ ሰዎች ጋር ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ብዙ ጊዜ አስገድዶ መድፈር የሚያጋጥመውና የሚመጣው ከሚታወቅ ሰው ነው፡፡
ተገዶ መደፈርንና ሌሎች የወሲብ ጥቃቶችን ለመከላከል እነዚህን ያድርጉ
- ሥራዎን በሚሰሩበት ጊዜ በተቻለ መጠን ከሌሎች ሴቶች ጋር ይሥሩ፤ ለብቻዎ ሲሆኑ ነው የሚጋለጡት
- ሚጠራጠሩትን ሰው አቤትዎ ውስጥ አያስገቡ፡፡: አቤትዎም ውስጥ ለብቻዎ አንዳሉ ለሰው አያሳውቁ
- ብቻዎን አይሂዱ፤ በተለይ በጨለማ ጊዜ ብቻ መሄድ አደገኛ ነው፡፡ የግድ ብቻዎን መሄድ ካለብዎት የፍርሃት ስሜት አያሳዩ፡፡ አንገትዎን ቀና አድርገው የድፍረት ስሜት እያሳዩ (በልብዎ ቢፈሩም) ፈጠን ፈጠን አያሉ ይራመዱ፡፡ይሄን ያየ ሰው ለማጥቃት ይፈራ ይሆናል
- የሚከተልዎት ሰው ያለ ከመሰልዎት ወደ ሌሎች መንገደኞች፣ ወደ ሱቅ ወይም በአካበቢው ወዳለ ቤት ይራመዱ፡፡ ወደኋላ ተመልሰው ጮክ በማለትና በመቆጣት ለምን አንደሚከታተልዎ ይጠይቁ
- በቦርሳዎ ውስጥ ለመከላከያ የሚሆን ነገር በቦርሳዎ ይያዙ፤ ለምሳሌ፤ ሚጥሚጣ፣ በርበሬ ከያዙ ሲጠቁ አይኑ ላይ በመበተን ሊያመልጡ ይችላሉ፡፡ ፊሽካ ካልዎትም ሊጠቅም ይችላል
- በኃይል ከተጠቁም ይጩሁ፤ ፊሽካ ካልዎት በደንብ ይንፉትና ድምፅ ያሰሙ፤ ይሄም ካላባረረው ቶሎ ብለው በሚጐዳ ቦታ መትተውት ለማምለጥ ይሞክሩ
- የሚያውቁት ዘመድ/ወዳጅ ቢሆንም ጥርጣሬ ካልዎት (ለምሳሌ ከአነጋገሩ፣ ከአስተያየቱ፣ ሰውነትዎን ከአነካኩ) ከዚህ ሰው ይራቁ፤ ከእንደዚህ አይነት ድርጊት እንዲቆጠብ በግልፅ ይንገሩት
- አለቃዎ፣ ተቆጣጣሪዎ፣ አስተማሪዎ፣ ሐኪምዎ፣ ባለስልጣን ወይም ሌላ በርስዎ ላይ ስልጣን ያለው ሰው የሚያሰቸግርዎት ከሆነ፤
- መጀመሪያ ይሄንን ድርጊታቸውን አንዲያቆሙ ግልፅ ያድርጉላቸው
- ሁለተኛ በዚህ አቋምዎ ፍራቻ እንደሌልዎትና የሚመጣውን መጋፈጥ አንደሚችሉ ያስረዱ (ሰዎቹ አራሳቸው ያን ጊዜ ሊፈሩ ይችላሉ)፡፡ ከመጀመሪያው በፍራቻ ወይም በይሉኝታ ዝም ካሉና ነገሮች ሥር ከያዙ ለእርስዎም በኋላ መፈናፈኛ ላያገኙ ይችላሉ
- ሦስተኛ አካባቢዎ ላሉ ሌሎች ሴቶች ችግርዎን ያካፍሉ፡፡አነርሱም እንደርስዎ አይነት ችግር ይኖርባቸው ይሆናል፤ አብራችሁ ችግሩን ልትጋፈጡም ተችላላችሁ
- አራተኛ ችግሩ የማያቆምና የሚቀጥል ከመሰልዎት ሁል ጊዜ አብርዎት የሚሆኑ ጓደኛ ይፈልጉ
- ልጆችዎ በወሲብ አንዳይጠቁ ይከላከሉ፤
- ለልጆችዎ እንዴት ወሲባዊ በሆነ መልክ ሊነኩ ሊታሻሹ እንደሚችሉ ያስተምራቸው፡፡ ወንድና ሴት ልጆችን (በተለይ ከ10-11 ዓመት በኋላ) ከተቻለ ለየብቻ እንዲያድሩ ያድርጉ
- ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው ልጆች ጉዳዩን በሚሰጥር ሳይዙ ገልጠው አንዲነግርዎት በግልፅ ያሳውቋቸው
- ወንድ አንዳስቸገራቸው ልጆች ከነገርምዎምት ያለምንም ጥርጣሬ እውነት እንደሆነ ይቀበሉ፡፡ አስፈላጊውን አርምጃ ይውሰዱ
በጥቃቱ ጊዜ ሊወስዷቸው የሚችሉ እርምጃዎች
- የሀይል ጥቃት ከተደረገብዎት፣ ከሁኔታው ለመላቀቅ የተቻልዎትን ያህል ይጣሩ፡፡ አይለምኑ፣ አይለማመጡ፤ የትም አያደርሰዎትም፡፡ የበለጠ ጉዳት ሊያመጣብዎት ይትችላል
- ቢደናገጡም፣ ተስፋ ሳይቆርጡ አሳቻ ጊዜ አንዳለ ይከታተሉ (ለምሳሌ ሰውየው ዘና ካለ፣ ዞር ካለ) በዚያን ጊዜ መልሶ ለማጥቃት ይሞክሩ
- በቀላሉ አጅ አይስጡ፡: ወንድሞች ዘመዶች አንዳልዎትና ይሄን ከሰሙ አጥቂው ሰው ላይ ከፍተኛ ጉዳት አንደሚያደርሱ ይናገሩ፣ ያስፈራሩ
- ሀይል ጥቃት የሰነዘረው የሚያውቁት ሰው ከሆነ አንዴት መጥፎ ነገር አየሠራ እንደሆነ ፣ እንዴት እየጐዳዎት እንደሆነ ይግለፁለት
- ኃይለኛው ሰው የማያውቁት ግለሰብ ከሆነ በጥንቃቄ ያስተውሉ፤ በኋላ ለፖሊስ ምን አይነት ሰው አንደሆነ ለመግለፅ ይረዳዎታል
- ያሉበትን የአደጋ መጠን ያመዛዝኑ፤ ለምሳሌ፤ በጦርነት ወቅት የሚደፍርዎት ወታደር ለእርስዎ ነፍስ ምንም ግድ የማይሰጠው ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህን ጊዜ ህይወትዎን ማትረፍ ቅድሚያ ያስፈልገው ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ኮንዶም አንዲጠቀም ልመና ወይም ማሳሰብ የሚያስፍልግበትም ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡
ተገደው ከተደፈሩ ወይም ከወሲብ ጥቃት በኋላ
- ቅርብ ለሆነ ለሚያምኑት ሰው ጥቃትዎን ይናገሩ፤ ምክር ይጠይቁ፡፡ ብዙ ጊዜ ባለቤትዎ ወይም ወላጆችዎ በጥቃቱ አነርሱም በጣም ስለሚረበሹ እርስዎን ለመርዳት አይችሉ ይሆናል፡፡ ከእነርሱ ሌላ አርስዎን በፅሞና የሚያዳምጡ፤ የእርስዎ ችግር የሚገባቸው፣ ሚስጥርዎን የሚጠብቁ፣ ከፈለጉ ደግሞ ፖሊስ ጣቢያ፤ ሐኪም ቤት፤ ወዘተ አብርዎት መሄድ የሚችሉ ዘመድ/ጓደኛ ቢሆኑ ይመረጣል
- ለፖሊስ ለማሳወቅ ውሳኔ ካደረጉ ጊዜ ሳይጠፉ ወዲያውኑ ሄደው ሪፖርት ያድርጉ፡፡ ይሄን ከማድረግዎ በፊት መረጃ ስለሚያስፈልግ አይታጠቡ፣ ልብስዎችዎንም በቦርሳ ይዘው ለፖሊስ ያሳዩ፡፡ በሕክምና ባለሙያም አስፈላጊው (በተለይ ከብልትዎ አካባቢ) ምርምራ አንዲካሄድልዎ ይጠይቁ
- ወደ ፖሊስ ጣቢያ ለመሄድ ካልፈለጉ ወይም በቶሎ ለመሄድ ካልቻሉ ግን ወዲያውኑ ወደ ሕክምና ባለሙያ ሄደው ለእርግዝና፣ ለኤድስና ለሌሎች ወሲብ ነክ በሸታዎች መከላከያ ያግኙ፡፡ ሐኪሙ የመረመሩትንና ያዩትን ሁሉ በፅሁፍ አንዲያሰፍሩ ይጠይቁ፡፡ ለበኋላ የፖሊስ ማስረጃ ወይም ለሌላ ማስረጃ ሊያስፈልግዎ ይችላል
- እርግዝናን ለመከላከል እንዲያመች ከጥቃቱ በኋላ ወዲያውኑ (በተለይ ከ3 ቀን በፊት) አርምጃ መወሰድ አለበት፡ ይሄም ጊዜ አልፎ አርግዝናው ከተከሰተ ሁኔታውን ለሐኪም አስረድተው የፅንስ ማስወረድ አርዳታ ሊያደርግልዎት ይችሉ ይሆናል
- ኤድስንም ለመከላከል እንደዚሁ በ24 ሰዓት ውስጥ ሕክምና ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ መድሐኒት ሳያቋርጡ ከወሰዱ በሽታውን መከላከል ይችላሉ፡፡ ከ6 ወር በኋላ የኤድስ የደም ምርመራ አድርገው ሁኔታውን ሊያውቁ ይችላሉ፡፡ ከዚያ በፊት በምርመራ ማወቅ ያስቸግራል፡፡ ለማንኛውም ሁኔታው እስኪጣራ የወሲብ ግንኙነት ሲያደርጉ ኮንዶም በመጠቀም የባለቤትዎን ወይም የፍቅር ጓደኛዎን ከበሽታው ይጠብቁ
- ለሌሉች ወሲብ ነክ በሸታዎች (ለምሳሌ ቂጥኝ፤ ጨብጥ፣፤ ወዘተ) የሚሰጥዎትን መድሐኒትና ምክር በመከተል ሊከላከሉ ወይም ሊያክሙ ይችላሉ
- በኃይል ከተደፈሩ በኋላ በብልትዎ ላይ የመቁሰል፣ የመላጥ ወይም የመሰንጠቅ አደጋ ሊደርስብዎት ይችላል፡፡ ለዚህም የሐኪም አርዳታ ያስፈልግዎ ይሆናል፡፡ ቀላል ለሆኑ ቁስሎች ግን ለሰስ ባለ ንፁህ ውሃ ውስጥ ብልትዎን በቀን ሦስት ጊዜ መዘፍዘፍ ሊጠቅምዎት ይችላል፡፡ ብዙ ውሃ ይጠጡ፤ ሽንትዎ ከበዛ ቁስሉን ያጥብልዎታል፡፡ በተለይ እዚያ አካባቢ ጀርሞች አንዳይባዙና ኢንፌክሽን አንዳይመጣ ይረዳዎታል፡፡ ቁስሉ መግል ከያዘ፤ ሽታ ከመጣ፣ ሽንት ሲሸኑ ካቃጠልዎና ፈሳሽ ነገር ከማህፀንዎ ከወጣ ወዲያውኑ ለሐኪም ነግረው መድሐኒት ይውሰዱ
- ከባለቤትዎ ወይም ከፍቅር ጓደኛዎ ጋር የወሲብ ግንኙነት ማድረግ ካልቻሉ (ለምሳሌ፤ በቁስል ምክንያት) ወይም ካልፈለጉ (ለምሳሌ፤ ባደረብዎት የህሊና ችግር) ይሄንኑ አስረድተዋቸው ጊዜ ያግኙ
- ባለቤትዎ ወይም ጓደኛዎ በሁኔታው በመናደድ፤ በመጨነቅ ከእርስዎ ጋር ግንኙነት ለማድረግ አይፈልጉ ይሆናል፡፡ ለእርስዎም ይሄ ተጨማሪ ከባድ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ መዘጋጀት ይጠቅም ይሆናል
ከዚህም በተጨማሪ የደረሰብዎት ጥቃት ጭንቀት፣ መደበትና ሌላ የአአምሮ በሽታ ሊያመጣብዎት ይችላል፡፡ ይህ ከመባሱ በፊት ወደ አአምሮ ሐኪም ጋ ሄደው አስፈላጊውን ሕክምና አና መድሐኒት ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው