የመደበት ስሜት (ዲፕሬሽን)

የመደበት ፅንሰ ሀሳብ ሀዘን፣ ብስጭት፣ አለመደሰት ወይም መከፋት በሚባሉ አሉታዊ ስሜቶች የሚገለፅ ነው፡፡ አብዛኞቻችን በህይወት ዘመናችን የሆነ ወቅት ላይ ለአጭር ጊዜም ቢሆን በዚህ ስሜት ውስጥ ማለፋችን አይቀርም፡፡ አንድ ሰው የመደበት ችግር ወይም ህመም ተጠቂ ነው የሚባለው ግን የለት ተለት ህይወቱ በሀዘን፣ በብኩንነት፣ በንዴት፣ በመከፋት ወይም በመረበሽ ስሜት ረዘም ላለ ጊዜ የሚታወክበት ከሆነ ነው፡፡

የመደበት ስሜት አብዛኛውን ጊዜ እንደ ክብደቱ ደረጃ የሚለያይ ሲሆን ቀላል፣ መካከለኛ ወይም ከፍተኛ ተብሎ ይለያል፡፡ የችግሩ ክብደት ደረጃም (ይህ በሀኪሙ የሚወሰን ነው) በሚሰጠው ህክምና አይነት ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡

የመደበት ችግር ሦስት ዋና ዋና ገፅታዎች አሉት፤

  1. የሀዘን ስሜት ብቻ ሳይሆን ከዚያም የበለጠ የሚያደነዝዝ፤ ተስፋ የሚያሳጣ አይነት ስሜት መሰማት፤ የተሰፋ ቢስነትና ስሜት፤ ጭምትነትና ወትሮ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መታቀብ፤ በሞትና ራስን በመግደል ሀሳብ በተደጋጋሚ መናጥ
  2. ለወትሮው መሥራት የሚችሉትን ክንዋኔዎች ለማድረግ ሃይል/ብቃት ማጣት  የአካል ድካም ብቻ ሳይሆን፣ ሃሳብን መሰብሰብ ማቃት፤ ዝለትና አቅመ ቢስነት፤ የወሲብ ጣዕመ ቢስ መሆን፤ ለመተኛት መቸገር ወይም በቂ አንቅልፍ አለማግኘት፤ ቅብጥብጥነት፣ አርጋታ ቢስነትና መነጫነጭ
  3. ስለራስ ያልዎት አስተሳሰብ ዝቅ ማለት  ራስን ዋጋ ቢስ አድርጎ ማየት፣ ራስን መጥላትና ተገቢ ያልሆነ የህሊና ወቀሳ ስሜት፤ድንገተኛ የምግብ ፍላጎት ለውጥ (አብዛኛውን ጊዜ የሰውነት ክብደት መጨመርን ወይም መቀነስን ያካተተ)

ከአነዚህ ዋና ገፅታዎች ሌላ ሊከሰቱ የሚችሉ ምልክቶች ይኖራሉ፡፡ አንደ አካላዊ በሽታ (ለምሳሌ የጨጓራ ህመም) መስሎ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከአካል በሽታ ምልክት ሌላም የመጨነቅ ስሜትም አብሮ ሊታይ ይችላል፡፡ በትክክል አለማሰብ፣ የሌለ ነገር ማየት/ማሽተት ወይም አጓጉል አምነት መያዝ አብረው ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

በወጣቶችም ላይ ደግሞ ሃይለኛነት፣ አጥፊነት፣ መነጫነጭ፣ ከዘመድ/ቤተሰብ አለመቅረብ ወይም የትምህርት ውጤት አያሽቆለቆለ መምጣት ሊሆን ይችላል፡፡ አልፎ አልፎ ራሳቸውን አስከማጥፋት ስለሚደርሱ ወላጆች በአፋጣኝ ህክምና ማፈላለግ ይኖርባቸዋል፡፡

የመደበት ችግር ያለባቸው ህፃናት የአዋቂዎቹ አይነት ዋነኛ የስሜት ለውጦች ወይም ምልክቶች ላይታይባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህም በትምህርት፣ እንቅልፍና ፀባያቸው ላይ የሚታዩ ለውጦችን ማስተዋል ይገባል፡፡ ህፃን ልጅም በመደበት ስሜት ተጠቅቷል የሚል ጥርጣሬ በሚያድርብዎት ጊዜ ለሃኪም ማሳየት ጠቃሚ ርምጃ ነው፡፡

የሚከተሉት ሁኔታዎች የመደበት ችግር መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ፤

  • በቤት፣ በስራ ወይም በት/ቤት ውስጥ የሚከሰት መጥፎ አጋጣሚ (ለምሳሌ ከፍቅር ጓደኛ ጋር መለያየት፣ ከሰራ መባረር፤ ትምህርት መውደቅ ወይም የወላጆች ፍቺ) ሊሆን ይችላል
  • የጓደኛ ወይም የዘመድ ሞት
  • ለረጅም ጊዜ በህመም መሰቃየት ወይም በከፍተኛ በሽታ መጠቃት
  • የጤና ችግሮች ለምሳሌ የታይሮይድ ሆርሞን ማነስ፤ ካንሰር ወይም የጉበት ብግነት
  • የተለያዩ መድሀኒቶች ለምሳሌ ለእንቅልፍና ለከፍተኛ የደም ግፊት የሚወሰዱ
  • የአልኮል ወይም አደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት
  • ስር ሰዳጅ ውጥረት
  • ከማህበራዊ ህይወት መገለል (በተለይ በአድሜ በገፉ ሰዎች ላይ)
  • የንጥረ-ምግብ እጥረት (ለምሳሌ የፎሌትና ኦሜጋ-3 ፋቲ አሲድ እጥረት)
  • አንቅልፍ-ነክ ችግሮች

ሴቶች ከወንዶች በበለጠ በመደበት ችግር አንደሚጠቁና በተለይም በወጣትነት ዕድሜ ላይ አንደሚያጋጥማቸው የህክምና ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የመደበት ችግር ብዙ ጊዜ በቤተሰብ ደረጃ የመከሰት ዝንባሌ ያለው ሲሆን ይህም በዘር-ውርስ የሚመጣ ሊሆን ይችላል፡፡ በቤተሰባቸው ወይም በዘራቸው የመደበት ችግር ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ለችግሩ የመዳረግ ዕድል ቢኖራቸውም ችግሩ የሚቀሰቀስባቸው ግን አብዛኛውን ጊዜ በህይወታቸው ውስጥ አስጨናቂ ወይም አሳዛኝ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ነው፡፡

Add new comment